በሃገራአችን በርካታ የጦርነት ታሪኮች ቢኖሩም እንዳሁኑ ወጣት ሴቶችን በማደን አፍኖ የሚወስድ ሃይል እንደነበረ አልሰማንም። ከሰሞኑ የሰማነው የአስገድዶ መድፈር ወንጀል የሚያሳየን ሃገራችን ለህጻናትና ሴቶች ከበፊቱ በባሰ ሁኔታ አስከፊ ቦታ እየሆነች መምጣቷን ነው። ዱሮ የህንድ ፊልም፣ ልጅ ሆነን ስናይ በባህላቸው ቁጥብነት ህንዶች እኛን ይመስሉን ነበር። ዛሬ በአጉል ዘመናዊነት ህንድ ውስጥ ሴቶችን ባደባባይ በቡድን ሆነው የሚደፍሩና የሚጎዱ ጋጠወጦች በዝተዋል። ዘመናዊነት ምኞትን የሚፈጥረውን ያህል አቅምንም አብሮ አይፈጥርም። አቅም ያጣና ከባህሉ የተነቀለ ወንድ ደሞ ፍላጎቱን ሊያካክስ የሚነሳው ደካማ በሆኑትና የሱን ከለላ በሚፈልጉት ወገኖቹ በተለይም በህጻናትና ሴቶች ላይ ይሆናል።
ወገኔ ሆይ፦ ድሆች በሰላም የሚኖሩበትና ፍትህ የሚያገኙበት ሃይል የሚያገኙት ራሳቸው ከሚፈጥሩት ስርአት ውስጥ ብቻ ነው። ስለዚህ ህዝብ ባካባቢው ያለውን ችግር ለመፍታት ባካባቢው ካለው ሰው ጋር መነጋገር፣ መተባበርና የመንግስትን ስራ መቆጣጠር አለበት። ከሩቅ የሚመጣ መሲህ፣ ከውጭ የሚገኝ መፍትሄ የለም። የድሆችን ሰቆቃ ችላ እያለ ጉልበቱን የሚያሳድግ መንግስት ጠንካራ ከሆነ በኋላ ህልውናውን ለማስቀጠል የድሃ ዜጎቹን ህይወት መብላት ይጀምራል። ስለዚህ ካሁኑ ባጨብጫቢነት ሳይሆን በጠያቂነትና በሃቀኝነት አካባቢያዊ ትብብርን ማደርጀትና በተጨባጭ ችግሮች ላይ ተባብሮ መስራት ያስፈልጋል። ባካባቢ ጉዳይ የሌሎችን አጀንዳ ሳይሆን የራስን አጀንዳ መፈጸም ያስፈልጋል።
ይህ የኮሮና ቫይረስ ጊዜ ይህን ከመቸውም በላይ ከህዝቡ ይጠይቃል። ጎረቤትወ ጋር፣ ጓደኞችወ ጋር፣ አካባቢወ ካሉ ሰወች ጋር በግልጽ በመነጋገር እዛው አካባቢወት ያሉትን ችግሮች ለመንቀል ይስሩ! ግፍ ሲሰራ ተቆጡ፤ ተስፋወትን ሩቅ ባሉ ግለሰቦችና የፖለቲካ ተዋንያን ላይ አያሳርፍ። ስለችግርወ ሊያወሩ ቢችሉም፣ መጠነኛ ድጋፍ ሊያደርጉ ቢችሉም ችግርወን ለማስወገድ የሚችሉት እርሰወና አካባቢወ መሪ ሲሆኑ ብቻ ነው። ችግርወን የሚኖሩት አካባቢወ ካለው ሰው ጋር ነውና በርሰወ ጉዳይ ተዋናዩም ተስፋውም ያለው እዛው አካባቢወ ውስጥ ነው። ይህንን ካላደረጉ ህይወትወን የሚጎዱ ሌሎች የክፋት ተባባሪወች አካባቢወን ይወርሱታል። ስለዚህ ራስወን፣ ልጆችወንና ማንነትወን ለማስከበር የሚኖሩበትን አካባቢ ከሙሰኞችና ከሰነፎች፣ ከግብዞችና ከወንጀለኞች ለማጽዳት ይተባበሩ። የመከባበር፣ የመረዳዳትና ለእውነት የመቆም ባህልወን ያጽኑ።
አካባቢያዊ አንድነት የመልካም ህይወትና የብሩህ ተስፋ መሰረት ነው!!
አካባቢ የሃገርበቀል እውቀቶች መፍለቂያ ነው!
Comments