top of page

ክፍል 2 “መተንፈስ አልቻልሁም”፦ የነጭ ሉአላዊነት ስራት አለማቀፍ ገጽታወች

Updated: Jun 7, 2020



መግቢያ


ባለፈው ሳምንት ጽሁፌ ላይ የነጭ ሉአላዊ ስራት ምን እንደሆነና ከሃገራችን ጋር ያለው ትሥስር ምን እንደሚመስል ለመግለጽ ሞክሬአለሁ። በዚህ ሁለተኛ ክፍል ደሞ፣ መጀመሪያ ሉአላዊነት ምን እንደሆነና የስልጣን ልዕልና ምንጭ አስተሳሰብ ስለመሆኑ አብራራለሁ። ከዚያም የነጭ ሉአላዊ ስራትን የምተነትንበት መንገድ (method) ለምን በታሪክ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ አስረዳለሁ። ከዛም፣ የነጭ ሉአላዊ ስራት ታሪካዊ አነሳስ የነበረውን አለማቀፋዊ ሂደት ባጭሩ እገልጽና በመጨረሻ “ነጭ” የሚለው ቃል መቸና እንዴት የሰው ዘር መጠሪያ እንደሆነ አብራራለሁ። ዘመናችን በአሜሪካ ሃያልነት የሚመራና አሜሪካ ደግሞ በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ ብሄራዊ ማንነት ያላት ሃገር ስለሆነች ይህንን ትንታኔ መረዳት የዘመናችንን ፈተና ለመገንዘብና አዲስ ነገር ለማሰብ ያነሳሳ ይሆናል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ። አሁን ባለው የነጭ ሉአላዊ ስራት ተጠቃሚ የሆን ልሂቃን የዚህ ስራት አስኳል የሆነውን ዘረኝነት ከተለመደው የነጭና የጥቁር ግለሰባዊ ግኑኝነት ባሻገር እንድናየው ያስፈልጋል ብየ አምናለሁ። በጽሁፉ ውስጥ ጠቃሚ ናቸው ያልኋቸውን ማጣቀሻወች በሃይፐርሊንክ አስገብቻለሁ።

ሉአላዊነት ምንድነው?


በመጀመሪያ ሉአላዊነት የሚለውን ቃል ለምን እንደተጠቀምሁት ለጠየቁኝና ማስተካከያም ለሰጡኝም ወዳጆቸ ታላቅ ምስጋና እያቀረብሁ፣ እዚህ ላይ ድክመቴን ለመቀበል እፈልጋለሁ። ዋልተር ሚኞሎ ‘I am where i think’ እንደሚሉት፣ ‘ቋንቋችን የሚገልጸው የማንን ሃሳብ ነው?’ የሚለው ጥያቄ አእምሯዊ ዜግነታችን (locus of enunciation) የማን እንደሆነ ያሳብቃልና፣ ልናስብበት ይገባል። በተለይ አንድ ወዳጄ ‘ልዕልና’ ብትለው ያለኝን ተቀብያለሁ። ነገር ግን ከሉአላዊነት ጋር ሰፊ የትርጉም ልዩነት ያለው ሆኖ ስላልተሰማኝ፣ የቃሉን ጎደሎነት ታሳቢ አድርጌ ለማለት ያሰብሁት ትርጉም ላይ በማተኮር እቀጥላለሁ።

ሉአላዊነት ወይም ልዕልና የነጫዊ ስርአትን የሃይል ደረጃ ለመግለጽ የተጠቀምሁበት ምክንያት ‘የበላይነት’ የሚለው የተለመደ ቃል ሃሳቤን የሚገልጽ ስላልሆነ ነው። ብዙ አይነት የበላይነት መገለጫወች ሊኖሩ ይችላሉ። ልዕልና ወይም ሉአላዊነት ‘የበላይነት ከሚለው ቃል ከፍ የሚልበት ልዩ ትርጉም አለው። ልዕልና ህጋዊ ወይም ልማዳዊ በሆነ አግባብ ተቀባይነት ያገኘ የሃይል ከፍታ ነው፤ በተቋማት፣ በባህልና በአስተሳሰብ ይደገፋል። ልዩ የሚያደርገውና እኔም የፈለግሁት ዋና ነጥብ ይህ ነው፦ የልኡላኑን የበላይነት፣ ገዢወቹ ብቻ ሳይሆኑ ተገዢወቹም (ፈቅደው፣ ተገደው ወይም ተታለው) ተቀብለው ራሳቸው ላይ በመጫን ይተዳደሩበታል፤ ሳይነገራቸው ቦታቸውን ያውቃሉ። ሉአላዊነት በዋናነት የሚሰራው ከተገዢወቹ ስነልቦና ውስጥ በሚወጣ የታዛዥነትና የይሁንታ ሃይል ነው። ሉአላዊነት የሃይል ብቻ ሳይሆን የስልጣንና የስራት ዋና መገለጫ ነው። በሌላ አባባል ሉአላዊነት የተገዢወችን አስተሳሰብ በመግራት ላይ ይመሰረታል ማለት ነው። የሃይል ምንጩ አስተሳሰብ መሆኑ ብዙ አንድምታ ስላለው አስተሳሰብና ስልጣን ስላላቸው ግኑኝነት ትንሽ ላብራራ።


አስተሳሰብና ስልጣን


በማንኛውም የፖለቲካ አውድ ውስጥ ገዢወች በቁጥር ከተገዢወቻቸው እጅግ ያንሳሉ። በፖለቲካና በኢኮኖሚ የበላይነት ያላቸው ከበርቴወች ሁሌ ከ1% ብዙ አይበልጡም። በሌላ በኩል 99% የሚሆኑት (በውስጣቸው ከፍተኛ ልዩነት ቢኖርም) እየተገዙ ነው የሚኖሩት። ይህንን የተረዳው እንግሊዛዊ ፈላስፋ ዴቪድ ሂዩም The first Principle of government በተሰኘ ጽሁፉ ውስጥ ጥቂቶች ብዙወችን ረግጠው የሚገዙበት ተአምራዊ ዜዴ ምንድነው? ለሚለው ጥያቄ ሲመልስ “Force is always on the side of the governed, the governors have nothing to support them but opinion ብሎ ነበር። ይህ ማለት በማንኛውም ስራት ውስጥ የስልጣን ምንጭ አስተሳብ እንጅ ጉልበት አይደለም፤ ተገዶ ከሚንበረከክ ሰው ይልቅ በፈቃዱ የሚንበረከክ ሰው ለጌታው ዘለቄታዊ ታማኝ ይሆናል ማለት ነው። ይህ አስተሳሰብ ዲሞክራሲ አለን በሚሉት ብቻ ሳይሆን በአምባገነን አገዛዝ ስር ናቸው በሚባሉ ሃገሮችም እንደሚሰራ ኖአም ቾምስኪን ይናገራሉ


አምባገነኖች ለፕሮፓጋንዳ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡት ዋናው የሃይል ምንጫቸው ጉልበት ሳይሆን አስተሳሰብ መሆኑን ስለሚያውቁ ነው። መፎከር ያስለፍፋሉ፣ የመገናኛ ብዙሃንን ይቆጣጠራሉ፤ የአስተሳሰብ ተቃዋሚወቻቸውን ያሳድዳሉ፣ ያስራሉ፣ ይገርፋሉ ወይም ይገላሉ። ጠመንጃ ከያዙ ሰወች የበለጠ የህዝቡን አስተሳሰብ የሚቀይሩ ሰወችን የሚያሳድዱት የተገዢወቻቸውን የአስተሳሰብ ነጻነት ስለሚፈሩ ነው። በአጠቃላይ የእነሱን ስልጣን የሚደግፍ አመለካከት የህዝብ እምነት እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። በሃይል ብቻ የሚገዙ ከሆነ ደሞ ስልጣናቸው ልዕልና አለው ብሎ ለመናገር ያስቸግራል። ዋናው ነጥብ የስልጣን ልዕልና የሚመነጨው የገዢወችና የተገዚወች አስተሳሰብ ተመሳሳይ በሚሆንበት ጊዜ መሆኑን ማጤኑ ላይ ነው። እዚህ ላይ አንድ ማረቂያ ሃሳብ ልጨምር። ሁሉም ተገዢወች የገዢወችን ሃሳብ መጋራት አለባቸው ማለቴ አይደለም። ለምሳሌ እንደአሜሪካ ዲሞክራሲን እንከተላለን የሚሉ ሃገሮች ውስጥ ምርጫን ለማሸነፍ በቂ የሆነ ቁጥር ያለው ህዝብ (ለምሳሌ በነጭ ልእልና የሚያምኑ) ከገዢወቹ ጋር ተመሳሳይ የሆነ አስተሳሰብ ከያዘ፣ የስልጣን ልዕልና ሊቀጥል ይችላል።


የትንታኔ መንገድ፡ ታሪክና ንድፈሃሳብ


ባለፈው ሳምንት የነጮች ሉአላዊ ስራት መኖሩን እንጅ እንዴት እንደተፈጠረ ታሪካዊ ዳራውን አልዳሰስሁትም። ይህንን ከማድረጌ በፊት ሃሳቤን ስለማቀርብበት መንገድ (method) አንድ ሃሳብ ላንሳ። ብዙ ጊዜ አንድን እውቀት ስንማር ወይም ስንሰማ በሃሳቡ የትንታኔ መነሻ ላይ አናተኩርምል። እውቀቱ የሚነሳው ከታሪክ ነው ወይስ ከንድፈሃሳብ የሚለው ጥያቄ አንገብጋቢ ነው። ከንድፈሃሳብ (ቲወሪ) የሚነሱ የእውቀት ዘርፎች ውስብስቡን አለም አቃለው የማሳየት ችሎታ ስላላቸው አስደማሚ ይመስላሉ። ሆኖም፣ ከብዙሃኑ ህዝብ ታሪካዊና ነባራዊ ልምድ አንጻር ሲመረመሩ መሰረተ ቢስ ሆነው እናገኛቸዋለን። ለምሳሌ የፖለቲካ ሳይንስ ውስጥ የሆብስንና የሎክን ስቴት ኦፍ ኔቸር (State of Nature)፣ ወይም ኢኮኖሚክስ ውስጥ Tragedy of the Commonsንና scarcity የመሳሰሉትን ቲወሪወች ብንወስድ፣ እነዚህ ንድፈሃሳቦች በአብዛኛው የምድራችን ህዝቦች ውስጥ ታሪካዊ መሰረት የላቸውም። ከህይወት ተሞክሮ የመነጩ ሳይሆን በቢሆን የተመሰረቱ (game theory) ናቸው። ‘ስቴት ኦፍ ኔቸርን’ ብንወስድ- አሁን በሚኖርበት ህግና ስራት ውስጥ ብቻ መኖር የለመደ ሰው፣ ህግና ስራት ከሌለ 'ህይወት ጦርነትና እልቂት የተሞላበት ይሆናል' ብሎ ለማመን አይከብደውም። 'ትራጀዲ ኦፍ ዘ ኮመንስን' ብንወስድ- በግለሰበኝነት ላይ የተመሰረተ ማንነት ያዳበረና በካፒታሊስት ስራት ውስጥ የሚኖር ሰው 'የጋርዮሽ ስራት ውስጥ ብንኖር ሳንሰለጥን እንቀር ነበር' ብሎ ለማመን አይከብደውም። ግባቶች ውስን ናቸው ፍላጎቶች ግን ወሰን የላቸውም (theory of scarcity) የሚለውን የኤኮኖሚክስ ቢሆንታ (assumption) እንደመነሻ የተቀበለ ሰው፣ 1% የሚሆኑት ከበርቴወች ከሰበሰቡት ሃብት ላይ የፍትህ ጥያቄ አያነሳም። በተለይ ኢኮኖሚክስ ውስጥ ዛሬ ያሉት ገናና ሃሳቦች ከምራባውያን ውጭ ባሉት ህዝቦች ታሪክና ልምድ ውስጥ ተጨባጭ መሰረት የሌላቸው ፈጠራወች ናቸው። በንድፈሃሳብ እውቀት ላይ ዘለግ ያለ ሂስ ለማቅረብ እዚህ ጊዜ ስለማይበቃኝ ማስመር የምፈልገው ነጥብ በቲወሪ ላይ የተመሰረቱ “የቢሆን” እውቀቶች በዋናነት ከስልጣንና ከሃይል ጋር (power and knowledge) የተሳሰሩ መሆናቸውን ነው። የሚያገለግሉትም የነጭ ሉአላዊነት ያልሁትን የካፒታሊስት ስራት ነው።


ይህንን ማየት የምንችለው በታሪክ ላይ የተመሰረተ ትንታኔ ስንከተል ነው። ታሪክ በቲወሪና በጸሃፊወች ግላዊ ፍላጎት ሊበከል የሚችልበትን አጋጣሚ እንደማስጠንቀቂያ ወስደን፣ እነዚህን ሁለት የብክለት ምንጮች ሊያስወግድ በሚጥር መንገድ ልንጠቀምበት ይገባል። ስለካፒታሊዝም፣ ስለስልጣኔ ወዘተ ከማውራታችን በፊት፣ በማን የታሪክና የልምድ መነጽር እነዚህን ጽንሰሃሳቦች እንደምንማር መጠየቅ ያስፈልጋል። እንደእኔ፣ በምጽፍለት ማህበረሰብ ታሪክና ልምድ ላይ ያልተመሰረተ ትንታኔ ተገቢነቱ ለህይወት ሳይሆን ለስልጣን (power) ነው። ስለሆነም ታሪካዊ ማስረጃወችን መሰረት በማድረግ የነጭ ሉአላዊ ስራትን አነሳስና፣ የነጭነትን ልዩ አሜሪካዊ ገጽታ ለመቃኘት እሞክራለሁ። አሜሪካ ላይ የማተኩረው በፍሎይድ ግድያ መነሻነት ብቻ ሳይሆን በተለይ ከ2ኛው የአለም ጦርነት በኋላ አሜሪካ ምድርን በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ የምትገዛ ሃያል መንግስት (ኤምፓየር) ስለሆነች ነው። ይህ ስልጣኗ የተመሰረተበት የዘረኝነትና የካፒታል ስራት በመሸርሸሩና አማራጭና ፍትሃዊ የሃይል መሰረት ስላልፈጠረች ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቃለች። ይህ ቀውስ ወደምን እንደሚያመራ የሚወሰነው ዛሬ ሰወች በሚያደርጉት ነገር ነው፦ ወይ የተሻለ አማራጭ ይወለዳል፣ ወይም ወደከፋ ፋሺስታዊ አለም እናመራለን። በዚህ ሂደት ውስጥ እኛም ድርሻ አለን። የተሻለ አለምን ለመፍጠር፣ ለፍተን የገበየነው እውቀት ከአለማቀፉ የዘረኝነት ስራት ጋር የሚተሳሰርበትን ገመድ መበጠስ አለብን። ለዚህ ይረዳን ዘንድ የስራቱን ባህሪ በታሪክ መነጽር ለመዳሰስ እሞክራለሁ።

የነጭ ሉአላዊነት ታሪካዊ መነሻ


በምድራችን ሰባት ህጉሮች አሉ። ከነዚህ ውስጥ ትንሿ ከሆነችው የአውሮፓ አህጉር ውስጥ ጥንተ ታሪካቸው እዚህ ግባ የማይባል ልዩ ልዩ ጎሳወች ይኖሩ ነበር። እስከ 15ኛው ክፍለዘመን ማለቂያ ድረስ ከሌላው አለም የሚበልጥ ስልጣኔ አልነበራቸውም። ከቻይና፣ ከህንድ፣ ከአፍሪካ፣ ከአረብ፣ ከፋርስ፣ ከሞንጎል፣ ከቱርክ ወዘተ ከነሱ የበለጠ ስልጣኔና ሃይል ያላቸው መንግስታት ተነስተው ነበር። ሮማውያን ከነበሯቸው መቶ ሚሊዮን ባሮች ውስጥ በብዛት እነሱ ነበሩበት። ሮም ከወደቀች በኋላ በክርስትና ላይ የተመሰረተ አንድነት ፈጥረው የሃይማኖት ልዩነትን በማጥፋት ላይ የተመሰረተ ክርስቲያናዊ ማንነት (ክርስቲአንደም) መገንባት ጀመሩ። በውስጥ ኢንኩዚሽን በውጭ የመስቀል ጦርነት እያካሄዱ፣ ‘የሰይጣን አምላኪወች’ ያሏቸውን እያቃጠሉና በሰይፍ እየቀሉ የማንነታቸውን ድንበር በቀይ ደም አሰመሩ። በርካታ የጥንት ፈላስፎችንና ቤተመጻህፍትን አቃጠሉ። አክራሪ ክርስትናን የፖለቲካና የማህበራዊ ኑሮ መሰረት በማድረግ ከሮም በፊት ጀምሮ በነበረውን የእውቀቶች ብዝሃነት እንዴት እንዳወደሙት ከካትሪን ኒክሲ The Darkening Age መጽሃፍ ላይ ይመልከቱ። የካቶሊኮቹ መሪወች ብቻ ሳይሆኑ የፕሮቴስታንቶቹ መሪወችም በሃይማኖት ከነሱ የተለዩት እንዲጨቆኑ ይሰብኩ ነበር።


ስፔን፣ ፖርቱጋልና ደቡብ ፈረንሳይ ለብዙ አመታት በአረብ ካሊፌቶች ይገዙ ነበር። በ15ኛው ክፍለዘመን መጨረሻ ላይ አረቦችን ከስፔን አባረው እየተጠናከሩ ቢመጡም የብዙሃኑ ነጭ ገበሬወች (peasants) ኑሮ በበሺታና በድህነት የተጎሳቆለ ነበር። ፖለቲካዊና ማህበራዊ ህይወታቸው በአስከፊ የጭቆና ሰንሰለት የተቆራኘ ነበር። ብዙ ነጮች በአፍሪካውያን ጭምር በባርነት ይያዙ ነበር። ለምሳሌ ሰሜን አፍሪካውያን ከ1500 እስከ 1800 እ.አ.አ ባለው ጊዜ ከ1 ሚሊዮን እስከ 1.25 ሚሊዮን የሚደርሱ አውሮፓውያንን በባርነት ይዘው እንደነበረ በጥናት ተረጋግጧል። በዚህ የBarbary Slave Trade ጊዜ በያመቱ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያን አውሮፓውያን በሰው ሃይል በሚገፉ ተንቀሳቃሽ ተሽከርካሪወች ላይ በባርነት (galley slavery) ወይም በቅምጥነት እስላሞች ጌቶቻቸውን እያገለገሉ በሞሮኮ፣ ቱኒዚያ፣ አልጀርስና ሊቢያ ይኖሩ ነበር። Paul Baepler የFernand Braudelን ምርምር ተንተርሶ እንደጻፈው፣ አልጀርስ ብቻ ከ1621 እስከ 1630ወቹ ድረስ ከ20000 እስከ 27000 ያውሮፓ ክርስቲያን ባሮች እንደነበሯት ጽፏል (p.3)።


እንግዲህ አንዳንድ ተዋሪወች እንደሚሉት ከሌሎች ቀድመው የሰለጠኑ ሳይሆን፣ እንደማንኛውም ሌላ ህዝብ በባርነት እየተያዙና በጦርነት እየተሸነፉ ሲኖሩ ቆይተው በ1492 በኮሎምበስ መሪነት አሜሪካን ከባለቤቶቹ ህንዶች ከዘረፉ በኋላ ሃይላቸው በፍጥነት እየጨመረ የመጡ ናቸው። ወርቅና ብር ብቻ ሳይሆን አህጉራትና ህዝቦችን ሳይቀር ዘረፉ። እምነታቸውንና ባህላቸውን በተገዢወቻቸው ላይ ጫኑ። የባሪያ ነጋዴነትን አስፋፉ። በሂደትም በሃይማኖት ላይ የተመሰረተው አንድነታቸው በዘር ላይ ወደተመሰረተ አንድነት ተሸጋገረ። ይህ ሽግግር ዱሮ የነበረውን የባርነትን ትርጉም በመቀየር የነጭ ሉአላዊነት የምለው ስራት ዋና መሰረት ሆነ።


ከ17ኛው ክፍለ ዘመን በፊት፣ "ባሪያ" "(ስሌቭ)" የሚለው ቃል በብዛት በባርነት ይያዙ ከነበሩት የስላቭ ጎሳወች የተወሰደ ነበር። ባርነት በሁሉም የአለም ክፍል የነበረ ልማድ ነበር። መጽሃፍ ቅዱስ ሳይቀር እንደሚነግረን ዮሴፍ ለባርነት ተሽጦ ነበር፤ ባሮች ሆይ ለጌቶቻችሁ ተገዙ ተብሎ ነበር። ባሪያው የነበረው ዮሴፍ የግብጽ ገዢ ለመሆን በቅቷል። በአይሁድና በእስልምናም ባሮች ባማካይ ከ6 አመት በኋላ ነጻ እንዲሆኑ ይደረግ ነበር። የሮማው ንጉስ ጀስትኒያ ባሮች ሰው ስለሆኑ መብት እንዳላቸው ደንግጎ ነበር። አንዳንዴ ሰወች እዳቸውን መክፈል ሲሳናቸው ለተወሰነ ጊዜ ላበዳሪያቸው ሰው ባሪያ ለመሆን ይስማሙ ነበር። በጦርነት የተሸነፉና የተማረኩ ሰወች ከየትኛውም ዘር ቢገኙ ባሪያ የሚሆኑበት እድል ነበር። ነገር ግን ይህ የባሪያ ትርጉም ከ17ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ ከጥቁር ህዝቦች ጋር ብቻ እየተያያዘ መጣ። ልብ ይበሉ። የባርነት ትርጉም ነጻነት ያጣ ሰው ከመሆን ወደ ተንቀሳቃሺ የእቃነት ደረጃ የወረደው ከ17ኛው ክፍለዘመን ወዲህ ነው። የዚህ ለውጥ ጠንሳሾች ባለስልጣናት ቢሆኑም፣ የለውጡ ዋና ሃዋርያት የኢንላይትመንት ምሁራንና የኢንዱስትሪው አብዮት ሳይንቲስቶች ናቸው። በዚያ ዘመን ለነበረው ሰው ሰራሽና ኢፍትሃዊ ስራት ተፈጥሯዊ ምክንያት በመስጠት የጥቁሩን ህዝብ ክብር ከሰባዊነት በታች አወረዱት።


ያኔ የሃይማኖት ተጸኖ ቀዝቅዞ የሳይንስ ዘመን ሲጀመር አፍሪካውያን የሚገዙበት የኢኮኖሚ አመክንዮ ወደተፈጥሮ አመክንዮ ተቀየረ። የባርነት ትርጉም ከማህበራዊ አውድ ወጥቶ ሳይንሳዊ (biological) ትርጉም ተሰጠው። ለሃይማኖት ማስተማሪያነት የተሰሩት ዩንቨርስቲወች ብቸኛ የሳይንስ እውቀት አምራች ተባሉ። ሬኔ ዴካርት የእውነት/እውቀት ምንጩ ጭንቅላት ነው ባለው መሰረት ሰወች ልምዳቸውንና ታሪካቸውን ሳይሆን፣ የሳይንቲስቶቹ ጭንቅላት ያመነጨውን ሃሳብ ብቻ 'እውነት ነው' ብለው መቀበል ጀመሩ። የእውቀት ምንጭ የሰው ልምድና ታሪክ ሳይሆን ምሁራኖቹ ያቀረቡት ንድፈሃሳብ (ቲወሪ) ሆነ። ተፈጥሮ ክብሯ ወደቀ፣ ወደጥሬእቃነት (ኮሞዲቲ) ተቀየረች። የዳርዊንን ‘የዘገምተኛ ለውጥ’ መላ ምት ተከትለው፣ የነጭና የጥቁርን ጭንቅላት ናሙና እየመዘኑና እየለኩ በማወዳደር፣ የሰው እርከን የሚያወጡ የአንትሮፖሎጅና ሌሎችም 'የምርምር’ ዘርፎች ተከፈቱ። የባሪያ ነጋዴ የነበረው ጆን ሎክ የነጻነት ፍልስፍናን ለነጮች ብቻ የተገባ አድርጎ አቀረበ። ዘረኝነት ባህል ሆነ፡፡ ዩንቨርስቲወች ዘረኝነትን መሰረት ያደረገ ምርመር ይደረግባቸው ጀመር። ከነጭ ውጭ ካሉ ነገዶች ናሙና ተወስዶ ጥቁሮችም እንደእንሣት ለትርኢት (human zoos) ቀረቡ። ያለማደንዘዣ የቀዶ ጥገናና ሌላም ህክምና መለማመጃወች ሆኑ። የሰውነታቸው አካል ሳይቀር የነጮቹን ጎደሎ መሙያ ሆነ። ዘመናዊነት አፍሪካውያንን ወደ ጥሬ እቃነት ቀየራቸው። ነጮች ብቻ ሰው ሆነው ሌሎቹ ግን ማነጻጸሪያወች ሆኑ። በዚህ መንገድ ልሂቃኑ የፈጠሩት 'ነጭ ሰው' የመብት ባለቤትና የምድር ገዢ ተባለ። ይህ የሰው ትርክት ጥቁሮችን አይመለከትም ነበር። በብዙ መንገድ የተከፋፈሉትን ነጮች ግን የአንድነት ስሜት ፈጥሮ የካፒታሊዝም ባለቤቶች እንደሆኑ አድርገው እንዲሰማቸው አድርጓል። በምን አይነት ምትሃታዊ ሃይል እኛም እራሳችንን በእነሱ የሰብእና መለኪያ እየለካን እንደኖርን ሲታሰብ በጣም ይደንቃል።

'ነጭነት' እንዴት ተፈጠረ?


ስለነጭ ምንነት ስጽፍ አንዳንዶች ስለነጭ ግለሰቦች እየጻፍሁ እንደሆነ አድርገው እንዳይተረጉሙት አሳስባለሁ። ነጫዊ ስራት ለነጮች በግለሰብ ደረጃ የሚሰጠው አንጻራዊ ጥቅም እንደተጠበቀ ሆኖ በዋናነት ግን የግለሰብ ጉዳይ ሳይሆን የስራት ጉዳይ ነው። ጥቂት ጥቁሮችም በዚህ ስራት ውስጥ ተባባሪና ተጠቃሚ ይሆናሉ። ምሁራን ራሳቸውን ከዘረኝነት ጋር ማቀላቀል ስለሚከብዳቸው ይህንን ትንታኔ አይደግፉትም። ዘረኝነት ልሂቃዊ ስሜትን ይኮሰኩሳል። ሆኖም በአለማቀፉ የዘረኛ ስርአት እንደእኛ ድሃ ህዝብ የሚጎዳ አይኖርምና የምናገለግላውን ስራት በስሙ ልናውቀው ይገባል እላለሁ።


እንደጃኩሊን ባታሎራ ጥናት ከሆነ ‘ነጭ’ የሚለው ቃል የዘር ስያሜ ሆኖ የተፈጠረው በሜሪላንድ ህግ አውጭወች በ1681 ነው። ከዚያ በፊት አውሮፓውያን በመጡበት ሃገር ይጠሩ ነበር እንጂ በጅምላ “ነጭ” ስያሜ አልነበራቸውም። በርካታ ጥቁሮች በባርነት ቢኖሩም፣ ሊቋረጥ የሚችልበት ሁኔታም ነበረ። ለምሳሌ የመሬት ባለቤቶች በኑዛዜ ወይም በፈቃዳቸው ባሮቻቸውን ነጻ ማድረግ ይችሉ ነበር። ባሮችም ነጻነታቸውን በገንዘብ መግዛት የሚችሉበት እድል ነበር። ጥቁሮች በባርነት ተገዝተው ስለመጡ ባሪያ ሆነው ይሰራሉ እንጅ በተፈጥሮ ጥቁር ሆነው በፈጠራቸው ምክንያት ለባርነት የተፈጠሩ ናቸው የሚል መደምደሚያ አልነበረም። ከባርነት በተለያየ መንገድ ነጻ ሆነው የሚኖሩ ጥቁሮች ነበሩ። በ1600 አካባቢ ከአውሮፓ በተለይም ከእንግሊዝ የሚመጡ ወዛደሮች እጅግ ይበዙ ነበር። እነዚህ ወዛደሮች ከ7-14 አመት የሚደርስ የጉልበት ስራ ለመስራት ኮንትራት ተዋውለው ነበር የሚመጡት። እነዚህ ነጮች በጥቁሮች ላይ ከቆዳቸው ቀለም ጋር የተያያዘ ልዩ ስሜት አልነበራቸውም። ሁሉም ለከበርቴወቹ (1%) ባለመሬቶች አገልጋዮች ነበሩ። የአገልግሎት ጊዜአቸውን ሲጨርሱ ነጮችና ነጻ ጥቁሮች ተመሳሳይ እድል ነበራቸው።፡ነጮች ጥቁሮች ጋር፣ ጥቁሮች ነጮች ጋር መጋባት ይችላሉ፤ ሁሉም የመምረጥና የመመረጥ መብት አላቸው፤ ጠመንጃ የመያዝና ራሳቸውን የመከላከል መብትም ነበራቸው።


እየቆየ ግን ከእንግሊዝ የሚመጡት የወዛደሮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቀነሰ፤ የመሬት ባለቤቶችም የጥጥ ማሳቸውን እንዲያለሙላቸው ያሉትን ወዛደሮች መብት ገድበው መበዝበዝ ቀጠሉ። የመሬት እጦትም ከፍተኛ ችግር ሆነ። ያኔ ናትናኤል ቤኮን የሚባል ሰው የተበሳጩ ጥቁርና ነጭ ወዛደሮችን እያስተባበረ አመጽ ቀሰቀሰ። ይህ አመጽ ቤክንስ ሪቮሉሺን ይባላል። በአመጹ ጥቁሮችና ነጮች በአንድ ላይ ተባብረው እኩል ተሳተፉ፤ አመጹ ከ1676 እስከ 1677 ተካሂዶ በእንግሊዝ ቅኝ ገዢወች በቁጥጥር ስር ቢውልም በገዢወቹ ላይ ከፍተኛ ስጋት ቀሰቀሰ። በተለይም ከልዩ ልዩ ዘር የመጡ ወዛደሮች (99%) ባንድ ላይ ሲተባበሩ የሚያደርሱት ጥፋት ወለል ብሎ ታያቸው። ያኔ ነው በ1664 ጀምሮ ነጮችንና ጥቁሮችን የሚከፍል ህግ ማውጣት የጀመሩት። በተለይ በ1681 ‘ነጭ’ የሚለው ቃል የአውሮፓ ዝርያ ላላቸው የወል መጠሪያ ሆኖ በህግ አውጭወቹ ተሰየመ። አመጹ እንደቆመ ህግ አውጭወቹ 1) ነጻ የሆኑ ጥቁሮች የፖለቲካ ስልጣን እንዳይዙ 2)ጥቁሮችና ህንዳውያን ከነጮች ጋር እንዳይጋቡ 3) ነጮች የወዛደርነት ጊዜአቸውን ሲጨርሱ መቋቋሚያ ንብረት፣ ጠበንጃና ባሩድ እንዲሰጣቸው 4) ጥቁሮች ግን ከባርነት ነጻ ቢሆኑም ምንም አይነት መሳሪያ እንዳይዙ 5) ጥቁሮች በነጮች ላይ ምስክር የመሆን መብት እንዳይኖራቸው። ይህን የመሰለ የከፋፍለህ ግዛ ህግ በብዙ ግዛቶች (states) ተደነገገ።


ይህ ህግ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቁርና ነጭን ሁለት ‘ተቃራኒ’ ዘሮች አድርጎ ደነገጋቸው። የጋብቻ ህጉ ዋና አላማ የጥቁርና የነጭ ደም እንዳይቀላቀል በመከልከል አውሮፓዊ ዝርያ ያለው ሰው ሁሉ አንድ ዘር እንደሆነ እንዲሰማው ማድረግ ነበር። ጥቁሮች ጠመንጃ እንዳይዙ የተደረገው የካፒታሊዝም አንዱ መሰረት የሆነውን ወንዳዊነትን ለመንፈግ ነበር። በነጮች ላይ የመመስከር መብት የተከለከሉት በነጮች ቢገደሉ ወይም ቢበደሉ በህግ መጠየቅ እንዳይችሉ ለማድረግ ነበር። የሚገርመው እነዚህ ህጎች ለነጮቹ ወዛደሮች አዲስ መብት አልሰጧቸውም፤ ይልቁንም የጥቁሮቹን መብት ከነጮቹ መብት በታች በማውረድ የበላይነትና ገዥ የመሆን ስሜትን ብቻ ነበር የፈጠረላቸው። ያኔ ከጥቁሮች ጋር እኩል አብረው አመጽ ላይ የተሰለፉ ነጭ ድሆች ከነዚህ ህጎች መውጣት በኋላ ራሳቸውን የከበርቴወቹ ስራት አካል አድርገው ማየት ጀመሩ። እንደከበርቴወቹ ሌሎቹን መግዛትና መርገጥ የሚችሉበት ነጭነታቸው የከፍታ ምልክት ሆናቸው። ድሃ ቢሆኑም ነጭ ስለሆኑና ከሌሎቹ ተለይተው የዜግነት መብት ስላላቸው አንድ ቀን እንደገዢወቹ ከበርቴወች ልንሆን እንችላለን የሚል ህልም መሰነቅ ቻሉ። ከመደብ ጠላቶቻቸው ጎን ተሰልፈው የመደብ አጋሮቻቸውን ረገጡ። በዚህም ምክንያት የከበርቴወቹ ስራት የእነሱ ስራት እንደሆነ አድርገው አመኑ።


የዘረኝነት ምንጭ እንግዲህ ይህ ነበር። እነዚህ ህጎች በልዩ ልዩ ግዛቶች ተደጋግመው ወጡ። የእንግሊዝ አገዛዝን ካስወገደው አብዩት በኋላ የመጀመሪያው ኮንግርስ ሲካሄድ የአሜሪካ የዜግነት ህግ ወጣ። በ1790 የወታው ህግ፣ ከየትኛውም አለም ወዳሜሪካ የመጣ ሰው ዜጋ መሆን የሚችለው ነጭ ከሆነ ብቻ ነው ብሎ ደነገገ።ይህ ህግ እስከ 1952 ድረስ ይሰራበት ነበር።፡አሜሪካ ውስጥ ዜጋ ለመሆን ነጭ መሆን ግድ ነበር። ሌላው ቀርቶ ነጭ ሴት የዜግነት መብት የሌለውን ወንድ ካገባች የዜግነት መብቷን ታጣ ነበር። ይህ ህግ ነጭ ሴቶች ለነጭ ወንዶች ብቻ እንዲሆኑ አድርጓል። ከቻይና፣ ከጃፓንና ሌሎችም የሚመጡ ሁሉ ዜጋ መሆን አይችሉም ነበር። የመሬት ባለቤትነት፣ የሰው ጉልበት፣ በህግ የሚወጡ ድንጋጌወች ሁሉ በዋናነት ለዜጎች (ለነጮች) ብቻ የተሰጡ ጥሬ ሃብቶች ሆኑ። ይህ ሁሉ የሚያስተላልፈው የነጭነት ልዩ ምንነት በሌሎች ዘሮች ዝቅ ማለት የተፈጠረ እንደሆነ ነው። ይህ ማንነት ከውስጡ የበቀለ የራሱ ልዩ መተሳሰሪያ ገመድ የለውም። ተከብሮ ለመቀጠል የሚችለው ሌሎቹን ዘሮች በማግለልና ዝቅ አድርጎ በማየት ብቻ ሆነ።


የባርነት ህግ ተሽሮ ጥቁሮች ነጻ ናችሁ ከተባሉ በኋላ ደግሞ የነጮችን የገዢነት ስሜት ለመጠበቅ ጥቁሮችን የሚጨቁኑ በርካታ ህጎች በተለይም በደቡቡ የሰሜን አሜሪካ ክፍል መዉጣት ጀመሩ። ብላክ ኮድና የጂም ክሮው ህጎች የሚባሉት በልዩ ልዩ ሰበቦች ነጮች ጥቁሮችን የሚቆጣጠሩበትንና የበላይነታቸውን የሚያስቀጥሉበትን ህጋዊ ከለላ ሰጣቸው። ለምሳሌ ስራና ቋሚ መኖሪያ የሌለው ጥቁር ዘዋሪ (‘ቫግራንት’) በሚል ተይዞ እንዲታሰር፣ ባሪያ የነበሩ መሳሪያ እንዳይዙ፣ በጥቁሮች ላይ እንጅ በነጮች ላይ እንዳይመሰክሩ፣ ነጮች ጋር እንዳይጋቡ መከልከል ቀጠሉ። መናፈሻወች፣ የቀብር ቦታወች፣ ምግብ ቤቶች፣ ቲያትርቤቶች የነጭና የጥቁር በሚል ተለዩ። በርካታ ጥቁሮች በልዩ ልዩ ተልካሻ ምክንያት በደቦ ይገደሉ ነበር፤ ሃብታቸውና ንብረታቸው ይወድም ነበር። ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው እንግዲህ፣ የመብት እንቅስቃሴ (civil rights movement) ከ1950 ጀምሮ ተደርጎ ህጎች የተሻሻሉት። ባህሉ ግን አልተቀየረም። ህጎቹ የሚተገበሩበት መንገድ የነጭን የበላይነትን በማይለውጥ መንገድ ብቻ ሆነ። እስርቤቶቹ፣ የመኖሪያ ሰፈሮቹ፣ የስልጣን ቦታወቹ የዘር ልዩነትን አሁንም ድረስ ያንጸባርቃሉ። ከጥቂት ዘመናት ወዲህ በተለይ በርካታ ነጮች ሃገራቸውን የተቀሙና ሃይላቸውን ያጡ መስሎ ይሰማቸዋል።


እዚህ ላይ ነጭንና ጥቁርን የማይደባለቁ ዘሮች አድርጎ የተፈጠረውን የጋብቻ ህግ ውጤት ማስተዋል ያስፈልጋል። የነጭነት ማንነት ከተፈጠረባቸው መንገዶች ዋናው ከጥቁሮች ጋር መጋባትን የሚከለክለው ህግ ነው ብያለሁ። ይህ ህግ የዘር ልዩነትን ተፈጥሯዊ (ባዮሎጅካል) አመክንዮ በመስጠት አሜሪካ ውስጥ ለ300 አመት ተሰርቶበታል። አሜሪካ ብቻ ሳይሆን ከፋፍሎ የመግዛት ጥበብን የተካኑት እንግሊዞች በሰፈሩበት አውስትራሊያና ካናዳም ጭምር ተሰርቶበታል። ይሁንና በርካታ ነጭ ወንዶች ከጥቁር ሴቶች ሲወልዱ የሚከሳቸው አልነበረም። ነጭ ሴቶች ግን ይህንን ከፈጸሙ ይከሰሳሉ፣ ያገቧቸው ወንዶችም አካላዊ ጥቃት ያጋጥማቸዋል። ይህ ማለት የጋብቻ ህጉ ነጭ ወንዶች በሁሉም ሴቶች ሰውነት ላይ ነጻነት እንዲኖራቸው ያደረገ ነበር። ሌላው ልብ ሰባሪ ጉዳይ ከነጭና ከጥቁር የተወለዱ ህጻናት እጣ ፈንታ ነበር። ብዙ ጊዜ ጥቁር ሴቶች ከነጭ የሚወልዱትን ልጆቻቸውን የማሳደግ መብቱ አልነበራቸውም። በተለይ የአውስትራሊያ መንግስት ከወላጆቻቸው ቀምቶ መዋእለ ህጻናት ወስጥ እንዲያሳድጋቸው ተወስኖ ለ60 አመታት ተሰርቶበታል፤ መቶ ሚሊዮን ህጻናት በፖሊስ ታድነው ከእናታቸው ጡት ተነጥቀው መንግስት ካዘጋጀው የማሳደጊያ ጣቢያ ገብተዋል። በካናዳም መቶ ሃምሳ ሺህ ህጻናት ተመሳሳይ እጣ ደርሶባቸዋል። እነዚህ ህጻናት ያሳለፉትን የግፍ ህይወት እዚህ መዘርዘር አይቻልም። የዚህ ሁሉ ድርጊት ዋና አመክንዮ የዘር ልዩነት የጥቂቶቹን ነጭ ከበርቴወች ከብዙሃኑ ነጭ ድሆች ጋር በማስተሳሰር፣ የካፒታሊዝም ቋሚ ደጋፊ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። ካፒታሊዝም ምእራባውያን ውስጥ የድጋፍ መሰረቱን የጣለው በዋናነት በነጭ ሉአላዊነት እሳቤ ነው ማለት ነው።


መደምደሚያ


ይህ ሁሉ ወደሚነግረን የመነሻ ነገራችን እንመለስ። የነጭ ሉአላዊነትን መሰረት ያደረገው ስራት ከ1492 ጀምሮ በስፔን መሪነት፣ በእንግሊዝና ፈረንሳይ ተከታይነትና በአሜሪካ ጨራሽነት እነሆ እዚህ ላይ ደርሷል። ይህ ስራት ለጥቂት ከበርቴወች ታላቅ ሃብት የሰጠ ነው። ከገዥው መደብ ውጭ ያለውን ህዝብ ሁሉ ደሞ የተለያዩ ዘዴወችን በመጠቀም ከፋፍሎ በመግዛት ላይ ይገኛል። ከሁለተኛው ያለም፡ጦርነት ወዲህ፣ ይህ ስራት የሚመራው በአሜሪካ የፖለቲካ፣ የወታደራዊና የኢኮኖሚ የበላይነት ነው። አሜሪካ ውስጥ የስልጣን መሰረቱ ደግሞ የነጭ የበላይነት ነው። ዛሬ ግን፣ እንደምናየው የነጭነት ታሪካዊ ልእልና ፈተና ላይ ወድቋል። ዛሬ ምራባውያንን ካምፓኒወቻቸው ትተዋቸው ርካሽ ጉልበትና ጥሬእቃ ወዳለበት ሃገር ሄደዋል። ህዝቡም የሚመረተውን ምርት ለመጠቀም የሚያስችል የዱሮውን አይነት አቅም እያጣ ሆኗል። ካፒታሊስቱ ሃብቱን ይዞ ገሸሽ ሲልና 1%ቹ ሲከዷቸው ተበሳጭተዋል። በጋራ የቆሙበት መሰረት ሲፈረካከስ ስራቱን አፍርሰው ስራቱ የሰጣቸውን ማንነት እንዴት እንደሚያስቀጥሉት ማወቅ አቅቷቸዋል። ስለዚህ ስራቱን ሳይሆን የማንነታቸው ጠላት የመሰሏቸውን ስደተኞችና አናሳወች ጣታቸውን ቀስረዋል።


የላቲን አሜሪካ ሊቃውንት እንደሚሉት የ500 ዘመኑ የቅኝ መግዣ ሃይል የቆመበትን ቦታ እየቀየረ ነው። ከነጩ አለም እየወጣ ወደቻይና መሰል ሃገሮች እየገባ ነው። የነጭ ሉአላዊነት ወደቢጫ ሉአላዊነት ይቀየር ይሆን? ለውጡ የተሻለ አለም ይፈጥራል አይፈጥርም? የሚሉት ጥያቄወች የጭንቀት እንጂ የመፍትሄ ምንጭ አይሆኑም። የተሻለ አለም ለመፍጠር እኛ ምን እናድርግ የሚለው ነው የሚሻለው። ዛሬ የነጭ ሉ አላዊነት መሰረት የሆኑት አለማቀፍ እምነቶች እየተናዱ ነው። ካፒታሊዝም የፈጠራቸው የድሃ ሃገሮች ጥገኛ መንግስታት በብዛት እየኮሰመኑ ሄደዋል። በቴክኖሎጂ ሃይል የሚመራ አዲስ አለም ውስጥ ጥቂት የግል ኮርፖሬሽኖች የሉአላዊነት ባህሪ እያሳዩ ነው። እነዚህ ድርጅቶች በመንግስታት ላይ የተመሰረተውን የነጭ ሉአላዊነት በግል ኩባንያ ይቀይሩት ይሆናል የሚል ስጋት አለ። ሁሉን ነገር ወደዳታ በመቀየርና ለጥቅማቸው በማዋል ፋሽስታዊ ባህሪ የሚታይበት የዘረኝነትን አለም ሊያስቀጥሉ ወይም ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ይፈራል።


ይህ ሁሉ የሚያሳየን እውነታ፣ የእኛን አይነት ሃገሮች ስር ነቀል ለውጥ እንደሚያስፈልጋቸው ነው። ከዚህ በኋላ የነጭ ሉአላዊነትን በመከተል፣ በነጮች ቋንቋ በመማር፣ የነጮችን እውቀት በመሸምደድ የምንደርስበት ስልጣኔ የለም። በዚህ ጎዳና እንኳን ለህዝቡ ለተማረውም ተስፋ የሚሆን ነገር እየጠፋ ነው። ሌላው ቀርቶ የምድሪቱ የአየር ጸባይ መዛባት የሚያስከትለው አደጋ፣ ካፒታሊስታዊ ልማትን የሚከለክል ደረጃ ላይ ደርሷል። ስለዚህ፣ ዛሬ ወደራሳችን ለመመለስና ያለንን አጥንተን ለማሻሻል መነሳት የሚገባን ጊዜ ላይ ነን። የነጭ ሉአላዊነትን ከሃገራችን ትከሻ ላይ ለማውረድ ማድረግ ካሉብን ቀዳሚ ጉዳዮች አንዱ የትምህርት ቋንቋንና ይዘትን መቀየር ነው። ይህንን በተመለከተ ወደፊት በሌላ ርእስ ወደፊት እመለሳለሁ።

ከላይ በሃይፐርሊንክ ያልተጠቀሱ ማጣቀሻወች


Baepler, Paul, ed. White slaves, African masters: an anthology of American Barbary captivity narratives. University of Chicago Press, 1999.


Washington, Harriet A. Medical apartheid: The dark history of medical experimentation on Black Americans from colonial times to the present. Doubleday Books, 2006.

287 views0 comments
bottom of page