top of page

የካፒታሊዝም አጀማመርና፣ የሃገርበቀል እውቀት እጣ ፈንታ


በአንድ በኩል ምድራችን የፈርኦንን ጭካኔና የሂትለርን ክፋት ከትውልድ ትውልድ ትዘክራለች። በሌላ በኩል ደግሞ እጅግ ዘግናኝ የሆነውን የአሜሪካን ‘ህንዳውያን’ ጭፍጨፋ እስካሁን ደብቃ ይዛለች። የአሜሪካ የጥንት ባለቤቶች እጣ ፈንታ፤ የአዝቴክስ፣ የማያ፣ የኢንካ፣ የሜክሲኮ የስልጣኔ ባለቤቶች፣ ያለስማቸው 'ህንዳውያን የሚባሉት ጭቁኖች፣ ሳይገባቸው ለምድራችን የከፈሉት ዋጋ ምን ነበር? በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በየትኛውም ሁኔታ በነሱ ላይ የደረሰውን አይነት ጭካኔ አልተፈጸመም ብሎ መናገር ይቻላል። ባሮች እንኳን አገልግሎት እስከሰጡ ድረስ የፈረስና የውሻ ያህል እንዲሰሩ ሲባል እንክብካቤ ይደረግላቸዋል። እነሱ ግን ጫካ እንደሚመነጠረው፣ አውሬ እንደሚታደነው፣ አረም እንደሚነቀለው ከምድራቸው ተመንጥረው የተገደሉበት መንገድ የሰው ልጅን የህሊና ሚዝን ይረብሻል። አረመኔነት በክፉ መሪወች ብቻ ሳይሆን በራሳችን በሰውነታችን ውስጥም በዚህ መልክ ሊገለጽ የሚችል ሃይል መሆኑ እጅግ ያስፈራል። ህጻናትን፣ ሴቶችን፣ ምንም ያላደረጉ ህዝቦችን በእሳት አቃጥሎ፣ በውሻ አስበልቶ፣ በጅምላ ገሎ፣ ነው የምእራቡ አለም የገናናነት እርሾውን የቋጠረው። ይህ የተጀመረው በ1492 እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ክርስቶፎር ኮሎምበስ በተባለ ነፍሰበላ ሰው መሪነት ነበር። እስከ 1900 ድረስ የ100,000,000 ህዝብ ህይወት እንዴት እንዳለቀ ዴቪድ ስታነር The American Holocaust በተባለ መጽሃፋቸው አስፍረዋል።

- እዚህ ላይ የሚታዩት ፎቶወችና ይህ መጽሃፍ በስፔን ወታደሮች የተፈጸመውን ዘግናኝ ግፍ እዛው ሄደው ያዩ ባርቶሎሜ ዴ ላስ ካሳስ የተባሉ የካቶሊክ ቄስ የጻፉት ነው።፡ያውሮፓ ነገስታት ክርስቲያን ናችሁና ግድያውን አስቁሙ ብለው ለመማጸን ሰቆቃውን ጽፈውታል። አውሮፓውያን ግን፣ ያኔ በግድያው የተገኘው ትርፍ ስለጣማቸው ችላ አሉት፤ ዛሬም ደሞ መሬቱን የራሳቸው ህዝብ ስለሰፈረበት ታሪኩን ደመሰሱት። የተረፉትን ያገሩን ተወላጆችም እስካሁን ጨቁነው፣ አረመኔነት የተፈጸመባቸውን ጊዜአት እንደብሄራዊ ቀን ያከብራሉ። ዛሬ የእኛም ተማሪወች ሳይቀሩ ክርስቶፎር ኮሎምበስን እንደጀግና ሳይንቲስት እንዲማሩት ተደርገዋል። ኮሎምበስ ከጨፈጨፋቸው ህዝቦች ሃገር ላይ ሃውልት ተሰርቶለታል። የአእምሮ ባርነት ውስጥ የተነከረውና የአውሮፓን ሃሳብ ገልብጦ በማጥናት ብቻ እውቀት የሚገኝ የሚመስለው የዘመኑ የድሃ ሃገራት ተማሪም የምእራቡን አለም የተጣመመ ታሪክ እንደመጽሃፍ ቅዱስ ይሸመድዳል፤ እንደቁራን ይቀራል።


- ምእራባውያን ከ1492 በፊት ምድር ላይ የሚታወቁበት ጉልበት አልነበራቸውም። አውሮፓዊ ብቻ ያልነበረው የሮም ስርአት ወድቆ ነበር፤ ስፔንና ፖርቱጋል በአረቦች ይገዙ ነበር፤ ወደ እስያ ማለፊያ አጥተው በመስቀል ጦርነት እየተናጡ፣ በሃይማኖት ስም ጠንቋይና ከሃዲ ያሏቸውን ምስኪኖች እየገረፉና በእሳት እያቃጠሉ ጭካኔን የተለማመዱት አውሮፓውያን፣ እግራቸውን ገነት ከመሰለ ለምለም መሬት በኮሎምበስ መሪነት አሳረፉ። ከ1500 እስከ 1650 ባለው ጊዜ 181 ቶን (164,200 ኪ.ግ) ወርቅና 16000 ቶን (5,443,108) ብር ከአሜሪካ ወደአውሮፓ ተጭኖ እንደገባ ይፋዊ መረጃወች ያሳያሉ። የስፔንን ሃብት ያዩ ፈረንሳይና እንግሊዞችም ሰሜን አሜሪካን፣ ካናዳንና አውስትራሊያን ተቀራመቱ።


- ሰሜንና ደቡብ አሜሪካን፣ ካናዳን፣ አውስትራሊያንና ኒውዚላንድን ከባለቤቶቹ ህዝቦች ቀምተው፣ አፍሪካውያንን በባርነት፣ እስያን በቅኝ ግዛት ገዝተው፣ ዛሬም በተንኮለኛ የአለማቀፍ የገንዘብ ስራቶች ጥቅማቸውን እያስከበሩ ነው እዚህ የደረሱት። እኛ የነሱን ቋንቋና እውቀት ተምረን እንደነሱ እንሆናለን የምንለው በየቦታው እነሱን ለማገልገል ወደው ከገቡት ሃገሮች ውስጥ ስለተቀላቀልን ነው። በዚህ መንገድ አጓጉል ሆነው የቀሩ እንጅ ጫፍ የደረሱ አይገኙም። ሲጀመር 'ሳይንስ' ብለን የምንጠራውን ጥበብ እነሱ ለአለም እንዳበረከቱት ለማስመእል ብዙ ቢያደርጉም፣ ከነሱ የመነጨ አይደለም። ወደነሱ ሳናንጋጥጥ ልንማረው የሚገባ የሰው ዘር ሁሉ ስጦታ ነው። መጽሃፍ መጻፍ፣ መድፍ መስራት፣ ፍልስፍና፣ ሂሳብ ወዘተ ከነሱ የተጀመረ አይደለም። እነሱ ካሰለጠኑት አለም ይልቅ ያደኸዩትና ያጠፉት ይበልጣል ቢባል ማጋነን አይሆንም። ዱሮ፣ ድሃ ህዝቦችን በጅምላ ይገሉ የነበሩት ምእራባውያን፣ ዛሬ የድሃ ህዝቦችን ሃገርበቀል እውቀት በመግደል ላይ ናቸው። በመልክና በትውልድ እንደእኛ የሆኑ ነገር ግን በጥቅምና በአስተሳሰብ ምእራባዊ የሆኑ ያገር ውስጥ ተባባሪወች አሏቸው። እነሱ የሚያመርቱትን ብቻ እንድንጠቀም፣ ተፈጥሯዊ ምርት አምርተን ለውጭ እንድንሸጥና ዘረመላዊ ምረዛ የተደረገበትን ምርት እንድንመገብ፣ መጭው ትውልድ በእዳ ተነክሮ እንዲወለድና የሚሰራው ለእነሱ የሚከፈል እዳ እንዲሆን፣ አገልጋይ በሆኑላቸው መንግስታት ሃብታቸውን አስጠብቀው እየቀጠሉ ነው። ዛሬም በእንግሊዝኛ እንማራለን፤ ዛሬም እንደነሱ እንሆናለን ብለን እናምናለን፤ ዛሬም እነሱን እንደማስረጃ እየጠቀሱ የሚወሸክቱ ግለሰቦችን እንደአዋቂ እንቆጥራለን። ይህንን ሁሉ የምናደርገው ከድህነት የመውጣት ተጨባጭ ተስፋ ስላየን አይደለም። ይህን ሁሉ የምናደርገው እነሱ የጫኑብንን የውሸት ትርክት ስላመን ነው። ይህንን ባዶ ተስፋ የሚሰብኩን ልሂቃንን ስለምንከተል ነው። ይህ በደምና በዝርፊያ የተመሰረተ ስራት ጥቂቶችን በምድር እንዲሽከረከሩ፣ በሰማይ እንዲበሩ ሊያደርግ ይችላል፤ የሚብለጨለጩ ነገሮችን ሊያሳየን ይችላል። ጭቁኑን ህዝብ ግን ከአፈርና ከድንጋይ ላይ ጥሎ፣ ያለችውን መሬትና ገቢ እየቀማ ነው ይህንን የሚያደርገው። ይህ ስራት ከላይ እንደተገለጸው ካጀማመሩ ጀምሮ የዝርፊያ ስራት ነውና። ስለዚህ እናስተውል። ለደቂቃ ድምጻቸው ከጠፋው የምድራችን ምስኪናን ጫማ ላይ ቆመን እናስብ፣ ከገጠሩ ህዝባችን ህይወት ላይ ቆመን እናስብ፤ ማበዳችን ያልተገለጠልን እብዶች እንዳንሆን፣ በትህትና፣ በመከባበር ራሳችንን ለመሆን መክፈል ያለብንን መስዋእት እንክፈል። ለውጡ ማስተዋልና ያለንበትን ሁኔታ የተገነዘበ እንዲሆን እንጣር። ወደህዝባችን ስንመለስ ወደኋላ እየሄድን ሳይሆን ወደፊት እየተራመድን ነው። ምክንያቱም ሃገራችን ወደተቻለ እድገት የምትሄደው ብዙውን ህዝብ በሚያሳልፍ መንገድ እንጅ ልሂቃኑ በሚሄዱበት ጠባብ መንገድ አይደለም። የምንከፍለው አሁን ከምናጣው በእጅጉ ያነሰ ነውና!

- ሃገር በቀል እውቀት የህልውናችን መሰረት ነው!

ማጣቀሻ


Bartolomé de las Casas. A short account of the destruction of the Indies. 1552 http://www-personal.umich.edu/…/…/las_casasb2032120321-8.pdf


David E. Stannard. 1992. American Holocaust: Columbus and the Conquest of the New World. New York: Oxford University Press.

48 views0 comments
bottom of page